Tuesday, August 26, 2014

በጥፍሩም በጥርሱም ለስልጣን የሚተጋ መንግሰት …… እንዴት እንታገለው!!

በጥፍሩም በጥርሱም ለስልጣኑ የሚተጋን መንግስት በሁሉን አቀፍ ትግል መጣል አለብን ብለው ጠብ መንጃ ቢያነሱ ክፋቱ ምን ላይ እንደሆነ አልታይህም እያለኝ ነው፡፡ ለምን በጠብ መንጃ ፍልሚያ ስልጣን መያዝ እንዳለብኝ በግሌ ባይገባኝም አሁን ግን የኢህአዴግ ዓይነት መንግሰት ከደርግ እንዴት እንደሚሻል ማሰብ እያቃተኝ ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል ሰራዊት እንዴት እንገንባ ለሚለው ጥያቄ አፋጣኝ ምለሽ ካልሰጠን በስተቀር መንግሰት በግልፅ እየደገፈ ያለው በጠብ መንጃ ሊገዳደሩ የፈለጉት ነው፡፡ በሰላም ያልነውን ሰላም እየነሳን ይገኛል፡፡ መንግሰት ሆይ ሰላም እንድትሆን ሰላም ሰላም ለምንል ዜጎች ሰላም ሰጠን የምር የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡
በፍትሕ አደባባይ የፈለገውን ማድረግ የወሰነ መንግሰት በእጅ አዙር ደግሞ በየማተሚያ ቤቱ እየሄደ መፅሄትና ጋዜጣ ታትሙና ወዮላችሁ ማለት ተያይዞታል፡፡ ይህ ከህግ ሰርዓት ውጭ በየማተሚያ ቤቱ በግንባር እና በስልክ የሚደረገው ማሰፈራሪያ ከወሮበላነት ውጭ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ መንግሰት ለህዝብ ጥቅም ሲባል ክስ መስርቻለሁ ብሎዋል፡፡ ህዝቡ የሚለው ግን ሌላ ነው፡፡ መፅሄት መቼ ነው የሚወጣው ነው፡፡ በቃ!!! ፍርድ ቤት በመፅሔትና ጋዜጦች ላይ ቢፊልግ እግድ ቢፈልግ ይዘጉ እሰኪል ድረስ ምን የሚያጣድፍ ነገር መጥቶ እንደሆነ ባናውቅም የመንግሰት አሽከሮች በየጉራንጉሩ ባሉ ማተሚያ ቤቶች ደጃፍ እየዞሩ ማሰፈራራት ተያይዘውታል፡፡ ሹሞቻችን ይህን አላደረግንም ብለው እንደሚክዱ ባውቅም ይህን ዓይነት ወሮበላነት ማስቆም ካልቻሉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ መርሳት የለባቸውም፡፡ ስህተታችውን በአደባባይ ተችተን እንዲታረሙ የሚሰጣቸው ምክር ካንገሸገቸው የመጨረሻው ቀን ሲመጣ እንደሚጠየቁ ግን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ የወሮበላ አለቃነት ከወሮበላነት በላይ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ እነዚህን ወሮበላዎች አስቁሙልን ግልፅ አቤቱታ ነው፡፡ በየሳምንት ብዙ መቶ ሺ ብር ገቢ ያገኙ የነበሩ ማተሚያ ቤቶች በህጋዊ መስመር ሳይሆን በስልክና በቃል ከወሮበሎች በሚሰጥ ማሰፈራሪያ አጅ መስጠት እና ገበያ ማባረር ደግሞ የሚያስመሰግን ፍርሃት እንዳልሆነ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ የእያንዳንዳችን ፍርሃት ተደምሮ ነው እነርሱም ያለምንም ይሉኝታ ሊያሰፈራሩን ቤታቸውን ድረስ የሚመጡት፡፡ በወረቀት ትዕዛዝ ይድረሰኝ ለማለት ወኔ የሌለው ማተሚያ ቤት የሙት ዓመትና ተዝካር ወረቀት ሲያትም ይኖራታል፡፡
መንግሰት በሚዲያዎች ላይ በዶክመንተሪ ጀምሮት የነበረውን ወደ ፍትህ አደባባይ ያመጣውን የግል ሚዲያ አሁንም ገና አልበቃውም፡፡ በጥፍርም በጥርስም ሊዘለዝል እየባተተ ይገኛል፡፡ ኢትቪ ቤታችን ድረስ መጥቶ ለሆዳቸው ባደሩ ምሁራን ተብዬዎች እና ሹመኞች ሲሳደብ ያመሻል፡፡ የኮሚኒኬሸን ጉዳዮች መስሪያ ቤት ውስጥ ዳይሬክተር ናቸው የተባሉ ታምራት ደጀኔ የሚባሉ ኃላፊ መሰሪያ ቤቱ የመንግሰት ደሞዝ የሚከፈላቸው እኔ ጭምር በምከፍለው ግብር መሆኑን ዘንግተው የግል ፕሬስ ከተቃዋሚዎች ጋር ወግኖ እየሰራ ነው ብለው ከገዢው ፓርቲ ጎን ቆመው ሲከሱን አምሽተዋል፡፡ እኚህ ግለስብ ከተቃዋሚ ጎን መሰለፍ ማን ሀጥያት ነው እንዳላቸው አላውቅም፡፡ ተቃዋሚዎች በህግ ተመዝግበው የሚሰሩ ተቋማት እንደሆኑ እና የሚደግፋቸውም የሚቃወማቸውም ሰዎቸ መኖራቸው የሚጠበቅ መሆኑን ዘንግተውታል፡፡ ለነገሩ እርሳቸው የሚደግፉት ፓርቲ ነገ ተቃዋሚ የሚባል ወንበር ላይ ሊኖር እንደሚችል በተሰፋ ደረጃ ማሰብ አልቻሉም፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ በጥቅም የተገዙ አባላቶቹ ስልጣን ሲያጣ አብረውት እንደማይቆዩ ይረዳዋል- እርሳቸውንም ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግ በጥርስም በጥፍርም ፍልሚያ ውስጥ የሚገባው፡፡ አቶ ታምራት ደጀኔ እንዲረዱ የምፈልገው የግሉ ፕሬስ ተቃዋሚን ቢደግፍ አንድም ነውር እንደሌለው ይልቁንም ገዢውን ፓርቲ ለመደገፍ ገዢው ፓርቲ ብቁ እንዳልሆነ ማሳያ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በገንዘብ የሚደግፋቸው ነገር ግን ተደግፈው መቆም የማይችሉ “የግል” ተብዬ ሚዲያዎች እንደነበሩ መርሳት የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ ኢፍቲን፣ ዛሚ፣ ወዘተ
ሰኞ ነሃሴ 19/2006 በቀረበው ዶክመንተሪ ተብዬ ዘባተሎ ላይ ከለየላቸው የመንግሰት ሹሞኞች እስከ ዩኒቨርሲት መምህራን አልፎ ተርፎም አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴን ያሳተፈ ነበር፡፡ እርገጠኛ ነኝ ሀይሌ በሚዲያ ላይ ስለሚታዩ ግድፈቶች አጠቃላይ ሁኔታ ነበር የሚናገረው እንጂ አሁን ክስ ስለተመሰረተባቸው የግል ሚዲያዎች አልነበረም፡፡ ቆርጦ ቀጥሉ ኢቲቪ ግን ከህዝብ ጋር ሊያጋጨው ፍላጎቱን አሳይቶዋል፡፡ ሌላው ተዋናይ ዶክትረ አሸብር ወልደጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ ከብዙ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ነበር መልስ አሰጣጣቸው፣ የከሰሱትም ሪፖርተርን ነው፡፡ መንግሰት ደግሞ ከሪፖርተር ጋር ጉዳይ የለውም፡፡ እንዲከሱ ሲጠበቅ የነበረው ሌላ ነበር፡፡ ይቅር ብያለሁ ብለው አልፈውታል፡፡ የእርሳቸው ይቅር ባይነት ከመንግሰት ሰፈር ሊገኝ አልቻለም፡፡ ተበቃይ መንግሰት ለስልጣኑ ሲል በጥፍሩም በጥርሱም ከግል ሚዲያው ጋር ግብ ግብ ገጥሞዋል፡፡ ማን ያሸንፋል አና መቼ ወደፊት የሚታይ ነው፡፡
የቀረበውን ዘጋቢ ፊልም ማስታወሻ ይዜ ለሁሉም በስማቸው አንፃር ለመፃፍ ነበር የፈለኩት ይህን ዘባተሎ የበዛበት ድሪቷም ዘጋቢ ተብዬ ከዚህ በላይ ማለት ተገቢ ሆኖ ስለአልተመቸኝ ተውኩት …. ይህ ዘጋቢ ፊልም ተብዬ የተሰራበት ሙሉ ዶክመንት ለታሪክ እንደሚቀር ተሰፋ አለኝ፡፡ የዛን ጊዜ እንወቃቀሳለን፡፡ ምሁራን ተብዬዎች በእናንተ ተሰፋ ቆርጠናል ….. በእናንተ መምህርነት አንድም የተሻለ ጋዜጠኛ እንደማናገኝ፡፡ ለነገሩ ልጆቹ የአስተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የእኛም ናቸው እና በቤታችን ይማራሉ፡፡ ሀገር ማለት ልጄ ብለን እናስተምራለን፡፡


No comments:

Post a Comment